የዴንቨር የህዝብ ቤተ–መጽሐፍት ሁሉም ግለሰቦች ያለ አድልዎ፣ ማስፈራራት፣ የጉዳት ስጋት ወይም የግላዊነት ወረራ መረጃን የመድረስ እና ቤተ–መጽሐፍቱን በነፃ እና በእኩልነት የማግኘት መብታቸውን ይደግፋል። የዴንቨር የህዝብ ቤተ–መጽሐፍት ወዳጃዊ፣ ጨዋነት የተሞላበት እና አክብሮት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ቁርጠኛ ነው። የዴንቨር የህዝብ ቤተ–መጽሐፍት ግብ ለሁሉም የቤተ–መጽሐፍት ተጠቃሚዎች አስደሳች፣ ንፁህ እና ምቹ አካባቢ ማቅረብ ነው። ይህ አካባቢ የዴንቨር የህዝብ ቤተ–መጽሐፍት ሕንፃዎችን የውስጥ ክፍል እና ግቢውን እንዲሁም ምናባዊ ቦታዎችን ያጠቃልላል። የቤተ–መጽሐፍት አጠቃቀም ፖሊሲ የተነደፈው የሚከተሉትን ለማድረግ ነው፦
የቤተ–መጽሐፍቱን ንብረት ለመጠበቅ
የዴንቨር የህዝብ ቤተ–መጽሐፍት ስብስቦችን፣ መሳሪያዎችን እና ንብረቶችን ይጠብቃል፦ ሕንፃዎችን፣ ግቢዎችን እና ለአሁኑ እና ለወደፊቱ ተጠቃሚዎች ምናባዊ ቦታዎችን ጨምሮ። የቤተ–መጽሐፍቱን፣ የደንበኞችን፣ እና የሰራተኛ አባሎች ንብረት የሆኑ ማናቸውንም ቁሳቁሶች፣ መሳሪያዎች ወይም ንብረቶች ሆን ብሎ ማበላሸት፣ ማውደም ወይም መስረቅ የተከለከለ ሲሆን ህግን እንደመጣስ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ደህንነቱ የተጠበቀ እና ከስጋት ነጻ የሆነ አካባቢን ለማረጋገጥ
የዴንቨር የህዝብ ቤተ–መጽሐፍት ሚና ለደንበኞች እና ለቤተ–መጽሐፍት ሰራተኞች ደህንነቱ የተጠበቀ እና ከስጋት ነጻ የሆነ አካባቢን ማረጋገጥ ነው። ማንኛውንም የፌዴራል፣ የክልል ወይም የአካባቢ የወንጀል ህግ ወይም ደንብ የሚጥስ ማንኛውንም እንቅስቃሴ በዴንቨር የህዝብ ቤተ–መጽሐፍት ንብረት ላይ መፈጸም ወይም ለማድረግ መሞከር የተከለከለ ነው። የተከለከሉ ተግባራት ምሳሌዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ ነገር ግን በእነዚህ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም፦
- ወሲባዊ፣ አካላዊ፣ የቃል ወይም ሌላ አይነት ትንኮሳ
- ጉልበተኝነት
- ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያን በቤተ–መጽሐፍት ግቢ ውስጥ ይዞ መግባት
- ሕገወጥ ዕፆችን ይዞ መገኘት፣ መሸጥ ወይም በእሱ ተጽዕኖ ስር መሆን
- አጮልቆ መመልከት፣ ሰውን በመከታተል ወይም አስነዋሪ በሆነ ሁኔታ ገላን ማጋለጥ ባሉ ተግባራት ላይ መሳተፍ
- በቤተ–መጽሐፍት ንብረት ላይ መዋጮ መጠየቅ፣ መለመን ወይም ቁማር መጫወት
- ለጊዚያዊ ወይም በቋሚነት እገዳ ተጥሎ፣ የቤተ–መጽሐፍት ንብረትን ጥሶ ወይም ወደ ውስጥ መግባት
- የግል ንብረቶችን በመጠቀም መተላለፊያዎችን ማደናቀፍ
- የግል ንብረትን ችላ ብሎ መተው
- በአደጋ ጊዜ እና በመዝጊያ ሰዓት ከቤተ–መጽሐፍት ለቆ መውጣት አለመቻል
- ከሚከተሉት ውስጥ ከሦስቱ በላይ ወደ ቤተ–መጽሐፍት ይዞ መምጣት፦
- አንድ መካከለኛ መጠን ያለው ሻንጣ (ጎማዎች ያሉት ወይም የሌሉት)
- አንድ መካከለኛ መጠን ያለው ቦርሳ ወይም የጀርባ ሻንጣ
- አንድ የግል እቃ (የሴት የእጅ ቦርሳ/የላፕቶፕ ቦርሳ/ሰነድ መያዣ ቦርሳ)
ምቹ እና እንግዳ ተቀባይ አካባቢን ማቅረብ
የዴንቨር የህዝብ ቤተ–መጽሐፍት ምቹ እና እንግዳ ተቀባይ አካባቢን ያቀርባል። እርስበርስ መከባበር ሁሉንም ሰዎች የቤተ–መጽሐፍት ቁሳቁሶችን እና አገልግሎቶችን በደስታ እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል። የቤተ–መጽሐፍት ተጠቃሚዎች እርስበርሳቸው እና ከቤተ–መጽሐፍት ሰራተኞች ጋር አክብሮት እንዲኖራቸው እና ሌላ የቤተ–መጽሐፍት ተጠቃሚዎችን የማያስተጓጉል ወይም የቤተ–መጽሐፍቱን መደበኛ ስራ የማያደናቅፍ ባህሪ እንዲያሳዩ እንጠይቃለን። የመረበሽ ባህሪያት ምሳሌዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ ነገር ግን በእነዚህ ብቻ የሚወሰኑ አይደሉም፦
- ስድብን፣ ጸያፍ ወይም አላግባብ የሆኑ ቃላትን መጠቀም፤ ይህም በአንድ ግለሰብ ላይ ያነጣጠሩ የጥል ቃላትን ጨምሮ፣ ያለገደብ ዘርን፣ ብሔርን፣ ጾታዊ ዝንባሌን፣ ጾታዊ ማንነትን ወይም ሌሎች የግል ባህሪያትን የሚመለከቱ ንግግሮችን ያካትታል።
- ሌሎች የዴንቨር የህዝብ ቤተ–መጽሐፍት ስብስቦችን፣ መሳሪያዎችን እና ንብረቶችን ሲጠቀሙ እና ሲገለገሉባቸው የሚረብሽ ምክንያታዊ ያልሆነ ድምጽ መፍጠር
- የጆሮ ማዳመጫ የሌላቸውን ድምጽ ያላቸው መሳሪያዎችን መጠቀም ወይም ሌሎችን በሚረብሽ የድምጽ መጠን የጆሮ ማዳመጫዎችን መጠቀም። ሌሎችን በሚረብሽ ሁኔታ ማንኛውንም የመገናኛ መሳሪያዎችን መጠቀም
- መሮጥ፣ መግፋት፣ መደባደብ ወይም መገፍተር
- በቤተ–መጽሐፍት ውስጥ ሮለር ስኬቶችን፣ ብስክሌቶችን፣ የስኬትቦርዶችን፣ ስኩተሮችን ወይም ሌላ ተመሳሳይ መሳሪያዎችን መጠቀም
- ምክንያታዊ የሰራተኛ ጥያቄን አለማክበር
ጤናማ እና ንጹህ አካባቢን መጠበቅ
የዴንቨር የህዝብ ቤተ–መጽሐፍት ለሁሉም የቤተ–መጽሐፍት ተጠቃሚዎች ጤናማ፣ ንፁህ፣ ከአልኮል ነጻ እና ጭስ አልባ አካባቢን ይጠብቃል። ሌላ ማሳሰቢያ እስካልተለጠፈ በስተቀር፣ የመክሰስ ምግብ ወይም ክዳን ያላቸውን መጠጥ ሌሎችን በማይረብሽ ሁኔታ በቤተ–መጽሐፍቱ የህዝብ ቦታዎች መጠቀም ይፈቀዳል። ንፁህ እና ንጽሕናው የተጠበቀ አካባቢ ለመፍጠር እንቅፋት የሆኑ ድርጊቶች የሚከተሉትን ምሳሌዎች ያካትታሉ ነገር ግን በእነዚህ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም፦
- አልኮል፣ ሲጋራ፣ ኢ–ሲጋራዎች፣ ቫፕ፣ ማሪዋና፣ የሚታኘክ ትምባሆ ወይም ሌላ ትምባሆ በሕዝብ ይዞታ፣ መጠቀም ወይም መሸጥ
- ቆሻሻን የሚፈጥር፣ ነፍሳትን ወይም አይጥና መሰል ተባዮችን የሚስብ፣ ሌሎች ደንበኞችን የሚረብሽ ወይም የቤተ-መጽሐፍቱ ንብረቶች ላይ ጉዳት በሚያደርስ ሁኔታ ምግብ ወይም መጠጥ መጠቀም
- መተኛት
- ጫማ ወይም ሸሚዝ አለማድረግን ጨምሮ ተገቢ ያልሆነ አለባበስ
- የጤና አደጋ የሚያስከትል የግል ንፅህና
- አገልግሎት የሚሰጡ እንስሳትን እና በልዩ የቤተ-መጽሐፍት ዝግጅቶች ወቅት የሚፈቀዱትን ሳይጨምር፣ እንስሳትን ወደ ቤተ-መጽሐፍት ሕንፃዎች ውስጥ ማስገባት
- መጸዳጃ ቤቶችን ለመታጠብ ወይም ልብስ ለማጠብ መጠቀም
የቤተ-መጽሐፍት አጠቃቀም ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ
የቤተ-መጽሐፍት አጠቃቀም ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ይከናወናል። የቤተ-መጽሐፍት ሰራተኞች እና/ወይም የዴንቨር ፖሊስ መምሪያ የተከለከሉ ተግባራትን እና ባህሪያትን ለማስቆም ጣልቃ ይገባሉ። የቤተ-መጽሐፍት አጠቃቀም መመሪያን የማያከብሩ ግለሰቦች የቤተ-መጽሐፍቱ ሕንፃን፣ ንብረትን ወይም ምናባዊ ቦታን ለቀው እንዲወጡ ሊጠየቁ፤ ለተወሰነ ጊዜ (ወይም በአንዳንድ ሁኔታዎች በቋሚነት) ከቤተ-መጽሐፍቱ ሊታገዱ፤ እንዲሁም በቁጥጥር ስር ሊውሉ ወይም ሌሎች ሕጋዊ እርምጃዎች ሊወሰዱባቸው ይችላል። በዴንቨር የህዝብ ቤተ-መጽሐፍት የተጣለውን ማንኛውንም እገዳ(ዎች) መጣስ በማንኛውም ህጋዊ መንገድ ሊፈጸም ይችላል፣ ይህም ያለገደብ በተገቢው ግለሰብ(ዎች) ላይ የፍትሐ ብሔር እና/ወይም የወንጀል ክስ ሊቀርብ ይችላል።
አንድ ግለሰብ ከቤተ-መጽሐፍ ከተታገደ፣ እገዳውን እንዲነሳለት ከቤተ-መጽሐፍ የደህንነት አስተዳዳሪ ጋር መገናኘት እና በማንኛውም የዴንቨር ህዝብ ቤተ-መጽሐፍ ንብረት ላይ ከመድረሱ በፊት ውይይት ማድረግ አለበት። ይህንን ውይይት ለማቀድ የደህንነት አስተዳዳሪውን በ720-865-1110 (ከሰኞ እስከ አርብ፣ ከ8:30 a.m.-3:30 p.m.) ይደውሉ። ከ18 ዓመት በታች የሆኑ የታገዱ ግለሰቦች ወላጆቻቸውን ወይም ህጋዊ አሳዳጊዎቻቸውን በ720-865-1110 ለደህንነት አስተዳዳሪው እንዲደውሉላቸው ማድረግ አለባቸው።
ከአንድ ዓመት በላይ ከቤተ-መጽሐፍ የታገደ ማንኛውም ደንበኛ ያንን እገዳ ለቤተ-መጽሐፍት ኮሚሽን ይግባኝ የማለት መብት ይኖረዋል። ይግባኙ በቤተ-መጽሐፍቱ የደህንነት ሥራ አስኪያጅ የተወሰነውን ውሳኔ ኮሚሽኑ እንደገና እንዲመለከተው የሚጠይቅ የጽሑፍ ማመልከቻ መሆን አለበት፤ ይህም ለተወሰደው እርምጃ ምክንያት የሆኑ ሁነቶችን ማጠቃለያ እና እገዳውን ለመቃወም የቀረቡ ምክንያቶችን ማካተት ይኖርበታል። የቤተ-መጽሐፍት የደህንነት አስተዳዳሪ በጥያቄ ውስጥ ያሉትን ክስተቶች እና ለውሳኔው የዳረጉትን ምክንያቶች በዝርዝር የሚገልጽ የጽሑፍ ሪፖርት (እና ከድርጊቱ ጋር የተያያዘ ሌላ ማንኛውንም መረጃ) ለኮሚሽኑ ያቀርባል።
ደንበኛው ኮሚሽኑ የእርሱን ቃል በግል ተገኝቶ እንዲያዳምጥ ሊጠይቅ ይችላል፤ ነገር ግን የቃል መግለጫ መፍቀድና አለመፍቀድ በኮሚሽኑ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ ይሆናል። ኮሚሽኑ ድርጊቱ ስለመፈጸሙ በቂ ማስረጃ ካለ፣ እንዲሁም ውሳኔው በሁኔታው ላይ ተመስርቶ ያለበቂ ምክንያት ወይም በዘፈቀደ የተወሰነ ካልሆነ፣ የቤተ-መጽሐፍቱ የደህንነት ሥራ አስኪያጅ ያስተላለፈውን ውሳኔ ያጸናል።
የዴንቨር የህዝብ ቤተ-መጽሐፍት አጠቃቀም ፖሊሲ
በዴንቨር የህዝብ ቤተ መፃህፍት ኮሚሽን፣ ኦክቶበር 19፣ 2017 ተቀባይነት አግኝቷል
ዲሴምበር 15፣ 2022 ተሻሽሏል